AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአማራ ክልል ሕዝብ እና አመራሩ ወደ አዲስ የመንቃት ምዕራፍ የተሻገሩበት የልዩ ዘመን መክፈቻ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ባካሄድነው የከፍተኛ አመራሮች የግምገማ መድረክ፤ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አፈጻጸምና ስትራቴጂካዊ ውጤቶች በጥልቀት ገምግመናል ብለዋል።

ይህ ምርጫ የክልላችን ሕዝብና አመራር ከጠላት መጠነ ሰፊ ሴራዎች ከፍ ብለው በመራመድ፣ ለክልሉ ዘላቂ ልማትና ሰላም በጠራ መስመርና በማይናወጥ አንድነት በመቆም የማይሻር ገድል የፈጸሙበት ነው ሲሉም አክለዋል።
ሕዝባችን በዚህ ምርጫ ያሳየው ወደር የለሽ የሰላም ቁርጠኝነት እና የዴሞክራሲ ብስለት፤ በክልሉ ላይ በባዕዳንና በባንዳዎች የተጋረጡ የጥፋት ማነቆዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲቀለበሱ አስችሏል ብለዋል።
በቀጣይም የክልላችንን እምቅ አቅም ለመጠቀም ሰላምን በዘላቂነት ማጽናት፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች በቁርጠኝነት መመለስ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለብን በግምገማችን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል በማለት ገልጸዋል።