AMN – ግንቦት 30/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን ውብ እና ከብክለት ነፃ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን እያስገኙ ይገኛሉ፡፡
በከተማዋ ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ እስከ አቃቂ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ድረስ የሚዘልቅ የ56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተተገበረ ነው፡፡
ለአብነትም ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ፣ እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ቀበና ባለው መስመር የሚከናወነው መጠነ ሰፊ የከተማ ትራንስፎርሜሽን፤ ከወንዞቹ ዳርና ዳር እስከ 50 ሜትር እንደሚዘልቅ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ፕሮጀክቱ የአረንጓዴ ኮሪደሮችን፣ የሕዝብ መሰብሰቢያና የመዝናኛ ስፍራዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ እንዲሁም የንግድ እና የከተማ ግብርና ማዕከላትን አቀናጅቶ የያዘ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም መሰል ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በዋናነት በውጭ ሀገር ባለሙያዎችና አማካሪዎች የሚሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የእነዚህ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የንድፍ (ዲዛይን) እና የትግበራ ስራዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች የተቀረጹና የተተገበሩ በመሆናቸው፤ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በከተማ ልማት ያላቸውን የመፈጸም አቅምና ብቃት በተግባር አሳይቷል፡፡
በኮንስትራክሽን፣ በኢንጂነሪንግ እና በአርክቴክቸር፣ በመልክዓ-ምድር ውበት ግንባታ፣ በሎጂስቲክስና ተያያዥ የሙያ መስኮች ለበርካታ ዜጎች አዲስ የስራ ዕድል በመፍጠር የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍን በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃት ችሏል፡፡

ከአረንጓዴ ኮሪደሮችና ከመዝናኛ ስፍራዎች ጎን ለጎን የከተማ ግብርና እና የንግድ ቦታዎች ተቀናጅተው መገንባታቸው ለነዋሪዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ አስገኝተዋል፡፡
ቀደም ሲል በቆሻሻ መጣያነትና ለጎርፍ አደጋ ስጋት የነበሩት የወንዝ ዳርቻዎች አሁን ላይ ለሽርሽር ምቹ ፣ ለሸማቾችና ለነጋዴዎች በቀላሉ መገበያየት የሚያስችሉ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና ማራኪ የገበያና የመዝናኛ ማዕከላት ሆነዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ