ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር 9ሺ 400 የሥራ እድል የሚፈጥር ስምምት ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ጋር ፈጸመ

You are currently viewing ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር 9ሺ 400 የሥራ እድል የሚፈጥር ስምምት ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ጋር ፈጸመ

AMN – ሰኔ 3/2018 ዓ.ም

የዓለም ባንክ ቡድን አባል የሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር (አይ ኤፍ ሲ)፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሆስፒታሊቲ ዘርፍ ክንፍ ከሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በኢትዮጵያ ያለውን የመስተንግዶ(ሆስፒታሊቲ) አቅም ለማስፋፋት አጋርነት መሥርቷል።

ይህ ኢንቨስትመንት ከ9ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ይደግፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቱሪዝም ፍሰትን ያጠናክራል፣ እንዲሁም ለወጣቶችና ሴቶች መደበኛ የሥራ ዕድል መንገዶችን ይከፍታል ተብሏል።

አይ ኤፍ ሲ ለሚድሮክ ኢትዮጵያ የሸራተን አዲስ እድሳትን እና በአዲስ አበባ አዲስ የሚገነባውን የሸራተን ሆቴል ፕሮጀክትን ለመደገፍ የ80 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል።

ቱሪዝም በመላው ኢኮኖሚ ውስጥ የሥራ እና የንግድ ሥራ መስመሮችን በመፍጠር ለሥራ ዕድል እና ለገቢ ጠንካራ ሞተር መሆኑን የገለጹት የ አይ ኤፍ ሲ የአፍሪካ ቀጣናዊ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢትዮጲስ ተፈራ ፣ ከሚድሮክ ጋር በአጋርነት መስራታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን የሚደግፍ እንዲሁም ለወጣቶችና ለሴቶች ዕድሎችን የሚሻሽል ነው ብለዋል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ ይህ ትብብር የሀገር ውስጥ የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግ እና በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ቀጣይነት እና ትርጉም ያለው ተፅዕኖ ለማሳደር ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review