AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ይፋዊ መግለጫ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ገዢው የብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ወንበር ማሸነፉን አስታውቋል።
ይህንኑ ተከትሎ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት መብራቱ አለሙ (ረ/ፕ/ር) ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ምርጫን ማሸነፍ የህዝብ አደራን መውሰድ በመሆኑ እንደቀላል ኃላፊነት ሊታይ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ በመስከረም ወር ላይ የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት በትኩረት ሊሰራባቸው በሚገቡ ዐበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያና ምክረ-ሃሳብ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችን ለማስወገድ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በውይይትና በድርድር መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በንፁሃን እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ የጸጥታ ስጋቶች በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ማህበራዊ መስተጋብር ስለሚያላሉ፣ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጠንካራ ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ ያሉት መምህሩ፣ በስራ እድል ፈጠራ ላይም ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአርሶ አደሩንና የኢንዱስትሪውን ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም የመሰረታዊ ሸቀጦችን አቅርቦት ማረጋገጥም ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አክለዋል።
በታችኛው መዋቅር (በወረዳና በቀበሌ) የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች መገታት እንዳለባቸው በማንሳት፣ በሁሉም የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ የሚሆኑበት ሁኔታ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት መምህሩ፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች መራዘም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ በመሆናቸው ክፍተት ያለባቸው የፍትህ ስርዓቶች መሻሻል እንደሚኖርባቸዉ አስረድተዋል።
በዚህ ምርጫ ወደ ፓርላማና ክልል ምክር ቤቶች የሚገቡ ተመራጮች የህዝብን ድምፅ በአግባቡ የሚያሰሙበት አሳታፊ የፖለቲካ ባህል መገንባት እንዳለበትና መንግስትም ለዚህ ተነሳሽነቱን መውሰድ እንደሚገባው አመላክተዋል።
ብዝኃነትን በሚያጠናክሩ እሴቶች ላይ በመስራት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚሳተፍባት ሀገር መገንባት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በታምራት ቢሻው