ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቀዳሚ መዳረሻነት የአዲሷ አዲስ አበባ ቱሪዝም ሽግግር

You are currently viewing ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቀዳሚ መዳረሻነት የአዲሷ አዲስ አበባ ቱሪዝም ሽግግር

AMN – ሰኔ 04/2018 ዓ.ም

ቀደም ሲል የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆን ብቻ የምትታወቀው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ፣ ዛሬ ላይ የውበት፣ የጥንካሬ እና የዘመናዊነት ተምሳሌት በመሆን ዓለምን በክብር መጋበዝ ጀምራለች።

የከተማዋን ገጽታ በዋናነት ከቀየሩት ሥራዎች መካከል የኮሪደር ልማቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

እግረኞችን፣ ብስክሌተኞችን እና አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ሰፋፊ መንገዶችን ያካተተ በመሆኑም ከተማዋን በእግር ለመጎብኘት እጅግ ምቹ አድርጓታል።

ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል በቆሻሻ ተሸፍነው የነበሩት የወንዝ ዳርቻዎች በሸገር ፕሮጀክት አማካኝነት ዛሬ ወደ ውብ የአረንጓዴ መናፈሻነት ተቀይረዋል።

እንደ ወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ታላቁ ብሔራዊ ቤተመንግስት፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የአድዋ ሙዚየም ያሉ ታላላቅ የቱሪስት መስህቦች መገንባትም የከተማዋን ድምቀት አሳድገውታል።

እነዚህ አዳዲስ ስፍራዎች ዓለም አቀፍ እንግዶች በከተማዋ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲያራዝሙ በማድረጋቸው፣ በሆቴልና በእንግዳ ተቀባይነት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የገበያ መነቃቃት ፈጥረዋል።

የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ መራዘምና የጎብኚዎች ቁጥር መጨመርም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ አድርጎታል።

እነዚህ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ስማርት እና ውብ በማድረግ፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን እና ሁነቶችን ይበልጥ እንድትስብ ተጨማሪ አቅም ፈጥረውላታል።

የልማት ሥራዎቹ ከቱሪዝም ዘርፍ ባሻገር ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ሰፊ ሚና አበርክተዋል።

በተለይም በፓርኮች ጥበቃ፣ በጽዳት፣ በአስጐብኝነት እና በተለያዩ የንግድ ሱቆች ውስጥ ለብዙ ሺህ ወጣቶችና ሴቶች አዲስ የገቢ ምንጭ መሆን ችለዋል።

ቀደም ሲል በከተማ አስተዳደሩ በቀረበው የ9 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንዳመላከተው አዲሷ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ እና የቱሪዝም መዳረሻነቷን ባሳደገ መልኩ የዘመናዊነት ተምሳሌት ሆና ትቀጥላለች።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review