ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ግምት ያለው የሞተር ዘይት የሰረቁ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

AMN- ሰኔ 8/2018 ዓ/ም

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ካዲስኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር ወይም ኖክ የዋጋ ግምታቸው 3 መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 200 በርሜል የሞተር ዘይት ለዊ ቢዩልድ ኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡት ከአንድ ግለሰብ ጋር ከስምምነት ላይ ይደርሳል።

በስምምነቱ መሰረት አሽከርካሪው መንጃ ፍቃድ እና ሊብሬ አቅርቦ እንዲሁም የተሽከርካሪውን ሰሌዳ አስመዝግቦ የሞተር ዘይቱ ቢጫንም ጭነቱ ኮይሻ እንዳልደረሰ ኖክ ያረጋግጣል። ጉዳዩንም ለአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ሪፖርት ያደርጋል።

ግለሠቡ ያቀረበው ሊብሬ እና መንጃ ፈቃድ ሀሰተኛ እንደሆነ እንዲሁም ጠፍቷል ተብሎ የተመዘገበ የሌላ ተሽከርካሪ ሰሌዳን አሽከርካሪው መጠቀሙን ፖሊስ ባደረገው ምርመራ አረጋግጧል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ባደረገው ብርቱ ክትትል አሽከርካሪውን ከኖክ ጋር ያገናኘውን ግለሰብ እና ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ተሳትፎ ያላቸውን አብዱልሠላም ወራኪ፣ አብዱራህማን ሀሰን፣ መሀመድ ቢላል፣ ደረጄ በቀለ፣ አብዱልሀፊዝ አብዱልሽኩር፣ ነጃ ካሚል የተባሉት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ንብረቱን ማስመለስ ችሏል።

ኤግዚቢቶቹ በሸገር ከተማ አሸዋ ሜዳ እና በቢሾፍቱ ከተማ እንደተገኙ ዋና ፖሊስ መምሪያው ገልጿል።

ፖሊስ በወንጀሉ ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ተጠርጣሪዎች ውስጥ ነጃ ካሚል የተባለው ከዚህ ቀደም በግድያና በዘረፋ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሲፈለግ እንደነበር ታውቋል።

ግለሰቡ በፖሊስ ላለመያዝ ሲሞክር ያሽከረክር በነበረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 17262 አማ መኪና ለማምለጥ ሲሞክር ጎማው በጥይት ተመቶ ተይዟል።

ተጠርጣሪው በወቅቱ መረጃ ለማጥፋት ሲል በእጁ ይዞት የነበረውን ውድ ዋጋ ያለውን ሞባይል ስልክ መስበሩ አደገኛ ወንጀል ፈጻሚ መሆኑን እንደሚያሳይ ፖሊስ አረጋግጧል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ምርመራውን በማጠናቀቅ በአቃቤ ህግ በኩል በወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት አድርጓል።

ዋና ፖሊስ መምሪያው ንብረቱን በህግ አግባብ ለናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር አስረክቧል።

በርክክቡ ወቅት የኖክ ስራ አስኪያጅ አቶ በኩሪያ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት ድርጅታቸው የመጡለትን ሰነዶች በተገቢው ሁኔታ ትክክለኛ ሰነድ መሆናቸውን ማረጋገጥ ሲኖርባቸው ሳያረጋግጡ ንብረቱን ለአሽከርካሪው መስጠቱ ክፍተት መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ስህተቱ እንዳይደገም ጥንቃቄ እንደሚደረግ ለኤ ኤም ኤን የተላከው መረጃ ያመላክታል።

ፖሊስ ሌት ተቀን ለፍቶ ንብረቱን በማስመለሱ አድናቆታቸውን እና የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review