የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል የወሰደውን ቁርጠኝነት የቀድሞ ሕወሓት ቡድን ራሱን ለዕኩይ ዓላማ ለማደራጀት ተጠቅሞበታል-አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

AMN ሰኔ 8/2018

የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልልን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል የወሰደውን ቁርጠኝነት ህልውናው ያከተመው ህገወጡ የቀድሞ የሕወሓት ቡድን ራሱን ለዕኩይ ዓላማ ለማደራጀት እንደተጠቀመበት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው ሕወሓት የቀድሞ ሊቀ መንበር የነበሩት አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የፌዴራል መንግሥት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማግስት የትግራይ ክልልን ጊዜያዊ አስተዳደር በማዋቀር ሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታን ለማፋጠን ከፍተኛ በጀት መድቦ ሲሰራ ቆይቷል።

ሆኖም ጦርነት ናፋቂው የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ቢፈርምም አደገኛና ህገወጥ ወታደራዊ አቅም እየገነባ መቀጠሉን አመልክተዋል።

የፌዴራል መንግሥቱ የዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ጥረቶች እንዳይሳኩ ጽንፈኛው የቀድሞ ሕወሓት ቡድን ተደጋጋሚ የማደናቀፍ ተግባራትን እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ወጣቶችን ለአስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በመዳረግ ስጋት እንዲያንዣብብ ማድረጉን በመጥቀስ፥ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በፅንፈኛ ቡድኑ አማካኝነት የሰላም ስምምነቱ ሲደናቀፍ በዝምታ መመልከቱን አውስተዋል።

የቀድሞ ሕወሃት ቡድን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ለክልሉ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ከመጠቀም ይልቅ ራሱን ለማደራጀትና የጥፋት ዓላማውን ለማሳካት በጊዜ መግዣነት ተጠቅሞበታል ብለዋል።

የቡድኑ አመራሮችም ከውጪ ጠላት በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ሕጻናትን ከወላጆቻቸው በመንጠቅ ጭምር አዲስ ኃይል አደራጅተው ወደ ዳግም ግጭት ለመግባት የተሳሳተ አቅጣጫ እየተከተሉ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ሕዝብም ልጆጁን ከግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ ለመታደግ ከክልሉ ውጭ ወደሚገኙ አካባቢዎችና በውጭ ሀገራት ጭምር በማሸሽ የቡድኑን ሕገ-ወጥ ድርጊት አጥብቆ እየተቃወመ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ፅንፈኛ ቡድን በመሰላቸት ተስፋ የቆረጡ ነባር ታጣቂዎችም ለቀው በመውጣት ቡድኑን መዋጋት መጀመራቸውን አንስተዋል።

የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ አካላት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተቋቋመውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ ግጭት የሚያስከትል መዘዝ እየፈጠሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለማት የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች፣ሌሎች ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የዚህን ፅንፈኛ ቡድን ሕገወጥ እንቅስቃሴ አጥብቀው ሊያወግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review