ፈረንሳይ ሴኔጋልን በማሸነፍ የዓለም ዋንጫውን ጀመረች

AMN ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

በምድብ ዘጠኝ የምትገኘው ፈረንሳይ ሴኔጋልን 3ለ1 በማሸነፍ የዓለም ዋንጫ ጉዞዋን ጀምራለች።

የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ፈረንሳይ በመጀመሪያው 45 በሴኔጋል ብልጫ ተወስዶባት ነበር።

ጥራታቸው ከፍ ያሉ የፊት መስመር ተጫዋቾችን የያዘችው አውሮፓዊቷ ሀገር በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀስ ችላለች።

ሦስቱን የማሸነፊያ ግቦችንም በዚሁ አጋማሽ በአምበሉ ኪሊያን ምባፔ (2) እና ብራድሊ ባርኮላ አማካኝነት አግኝታለች።

99ኛ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ያከናወነው ምባፔ ሁለቱ ግቦች የግብ መጠኑን 58 አድርሰውለታል። ይህም 57 ግብ ያለው ኦሊቬ ዢሩን በልጦ የሀገሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንዲሆን አስችሎታል።

የሪያል ማድሪዱ አጥቂ በዓለም ዋንጫ ብቻ ያስቆጠረውን ግብም ከጀርመናዊው ገርድ ሙለር ጋር እኩል14 አድርሷል። የሚበለጠው በሚረስላቭ ክሎሰ (16) ፣ ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ (15) ብቻ ነው።

የሴኔጋልን ብቸኛ ግብ ኢብራሂም ምባዬ አስቆጥሯል። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በቀጣይ ከኖርዌይ ጋር ሌላ ፈታኝ ጨዋታ ይጠብቃታል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review