የኢ-ክፍያ ሥርዓቱ በ24 ሰዓት ውስጥ በጀትን አንቀሳቅሶ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ

AMN- ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት በጀት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፋይናንስ ቢሮን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል።

ዘርፉ የከተማዋን ፈጣን ዕድገት የሚያሳይና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሰራሮች የተበራከቱበት መሆኑ ተገልጿል።

በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ በ2014 በጀት ዓመት 70 ቢሊየን ብር የነበረው የከተማዋ በጀት፣ በአራት ዓመታት ውስጥ ወደ 360 ቢሊየን ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል።

ይህ የ6 እጥፍ ወይም የ300 ቢሊየን ብር ግዙፍ ዕድገት የከተማዋን ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያረጋግጥ መሆኑን የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ350 ቢሊየን ብር በላይ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 71 ከመቶ የሚሆነው በቀጥታ ለዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች መዋሉን ጠቁመዋል።

ለዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ወደ 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በሽግሽግ እንዲመደብ መደረጉንም አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን እንደገለጹት፣ ቢሮው በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን በማከናወን ወደ ወረቀት አልባ አገልግሎት ተሸጋግሯል።

በከተማዋ አዲስ የኢ-ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ በመደረጉ፣ በ24 ሰዓት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ በጀትን በቀላሉ አንቀሳቅሶ ለመጠቀም የሚያስችል እጅግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ደስታ በበኩላቸው፣ የቢሮው የፋይናንስ እቅድና የተቋማት በጀት አደላደል ስኬታማ መሆን የከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በፍጥነት፣ በጥራትና በዓይነት በዝተው እንዲተገበሩ ማስቻሉን አስምረውበታዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሪፖርቱ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ቢያደንቁም፣ በቀጣይ መስተካከል ያለባቸውን አንኳር ጥያቄዎች አንስተው ከቢሮው አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ከተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከልም፣ በጥሬ ገንዘብ አጠቃቀምና አመዳደብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እና በጀትን ከአንድ ዘርፍ ወደ ሌላ ዘርፍ በማዛወር ሂደት ላይ የሚስተዋሉ የግልጸኝነት ጉድለቶች ይገኙበታል፡፡

ለቢሮ ኪራይ ከፍተኛ በጀት ከመመደብ ይልቅ ተቋማት የየራሳቸውን ህንጻ መገንባት የሚችሉበትን ስትራቴጂ መንደፍ የሚለውም ከተነሱ ነጥቦች መካከል ነው።

በአንዳንድ ቢሮዎች ላይ የሚታየው የበጀት ጉድለት በቀጣይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

አሁን የተመዘገበው ስኬታማ ተሞክሮ ተጠናክሮ በመቀጠል በ2019 በጀት ዓመትም የላቀ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚገባ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review