AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
መንግስት ለስፖርት ልማት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በየደረጃው በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት አመራሮች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በስፖርት ልማት እቅድ አፈፃፀም ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ፤ የኢትዮጵያ ስፖርት ወርቃማ ዘመን ላይ እንደሚገኝ በማንሳት መንግስት ለስፖርት ልማት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በየደረጃው በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል ብለዋል።

በመላው አገሪቱ 45 ሺህ 177 የሚሆኑ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚገኙም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ብቻ ከ2 ሺህ 500 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለወጣቶችና ለታዳጊዎች ለአገልግሎት ክፍት እንደተደረጉም ገልጸዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መክዩ መሃመድ በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲዮም ግንባታ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በስኬት መስተናገዳቸውን አክለዋል።
በምክክር መድረኩ የተጠሪ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የዘርፉ እና የስፖርት ማህበራት ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዘላለም አቢይ