AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን ሰላምና እፎይታ የሚያረጋግጥ፣ ለረጅም ጊዜ ከቆየውና ልዩነትን በኃይል ከመፍታት የሚያላቅቅ ልምምድ መሆኑን በተግባር የተረዳንበት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የምርጫ ቦርድ አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በመርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ለሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝብ በመመዝገብ፣ ብቁ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማሰማራት ውጤታማ ሥራ ላከናወነው የምርጫ ቦርድ ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን ሰላምና እፎይታ የሚያረጋግጥ፣ ለረጅም ጊዜ ከቆየውና ልዩነትን በኃይል ከመፍታት የሚያላቅቅ ልምምድ መሆኑን በተግባር የተረዳንበት ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በየሻምበል ምህረት