AMN – ሰኔ 19/2018 ዓ.ም
በሰው ልጅ የእለት ተእለት የአመጋገብ ልማድ ውስጥ ሳይታወቅ በከፍተኛ መጠን የሚወሰደው ስኳር፣ ለተለያዩ የጤና እክሎች ዋነኛ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን የሥነ-ምግብ ሕክምና ባለሙያዋ ኬብሮን ሰናይ ይገልፃሉ።
ባለሙያዋ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኅብረተሰቡ በፋብሪካ የተቀነባበረ ስኳር አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም ለስላሳ መጠጦች፣ ብስኩቶች፣ እንዲሁም በሻይና በቡና ውስጥ የሚጨመር ስኳር ለከባድ የጤና እክል መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ስኳር በተፈጥሮ የሚገኝ እና በፋብሪካ ተቀነባብሮ የሚቀርብ ተብሎ በሁለት እንደሚከፈል የገለጹት ባለሙያዋ፣ አብዛኛውን ጊዜ ከጤና እክል ጋር የሚያያዘው በፋብሪካ የሚመረተው የስኳር ዓይነት መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ የፋብሪካ ስኳር ሱስ የማስያዝ ባሕሪ ያለው በመሆኑ፣ አጠቃቀሙን መቆጣጠር ካልተቻለ የሰውነትን የጣፋጭ ፍላጎት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረው ይሄዳል። ይህም በቀላሉ ለማቆም እንደሚያስቸግር አብራርተዋል።

ከመጠን በላይ የተቀነባበረ ስኳርን መውሰድ ለአላስፈላጊ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ከጉበት ጋር ለተያያዙ የጤና እክሎች እና ለስኳር በሽታ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
በተጨማሪም ከመጠን በላይ ስኳር መውሰድ ለልብ ሕመም ተጋላጭነትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ጉበት ከመጠን በላይ የሆነውን ስኳር ወደ ስብ የሚቀይረው ሲሆን፣ ይህም የደም ቧንቧዎችን በመዝጋት ለደም ግፊትና ለልብ ድካም ይዳርጋል።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ፣ አንድ አዋቂ ሰው በቀን ውስጥ መውሰድ ያለበት ከፍተኛው የስኳር መጠን ከ25 እስከ 30 ግራም ብቻ ነው።
ሆኖም አሁን ባለው ልምድ አብዛኛው ሰው ይህንን ከተፈቀደው መጠን በላይ ስኳር በአንድ የሻይ ወይም የቡና ስኒ ውስጥ ብቻ ይጠቀማል።
ለአብነት ያህል፣ በአንድ የለስላሳ መጠጥ ጠርሙስ ውስጥ እስከ 40 ግራም የሚደርስ ስኳር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሙያዋ፣ ዳቦ ላይ የሚቀቡ እንደ ማርማላት ያሉ ጣፋጮች ተደምረው የሰዎች የእለት ተእለት የስኳር አወሳሰድ ልኩን እንዲያልፍ እንደሚያደርጉት አስረድተዋል።

በተለይ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት መውሰድ ያለባቸው ከአዋቂዎች ግማሽ ያህሉን ማለትም ከ12 እስከ 15 ግራም ብቻ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
ሕፃናት ከዚህ መጠን በላይ ጣፋጭ ምግቦችን የሚወስዱ ከሆነ፣ ለከባድ የጤና እክሎች ከመጋለጣቸውም በላይ የጥርስ ጤንነታቸው በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡ በፋብሪካ ከተመረቱ ጣፋጮች ይልቅ ተፈጥሯዊ የሆኑ ማጣፈጫዎችን መጠቀም ይገባል ያሉት ባለሙያዋ፤ በተፈጥሮ በማር፣ በፍራፍሬዎች፣ በአትክልቶችና በእህሎች ውስጥ የሚገኘውን ስኳር መጠቀም ለጤና ተመራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የፍራፍሬ ጭማቂዎችን ጁስ በሚዘጋጅበት ወቅት ተጨማሪ ስኳር ከመጨመር ይልቅ የፍራፍሬዎቹን የራሳቸውን ጣፋጭነት መጠቀም ወይም እንደ ዘቢብ፣ ቴምር እና ማር ያሉ የተፈጥሮ ውጤቶችን በመጠቀም በጣፋጭ መብዛት የሚከሰት በሽታን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል የሥነ-ምግብ ባለሙያዋ መክረዋል።
በረከት ጌታቸው