AMN- ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት ቀርተውታል።
ፕሮጀክቱ ከውኃ መሐንዲስነትና ኢኮኖሚያዊ ስኬት ባሻገር፣ በአፍሪካ ቀንድና በናይል ተፋሰስ ለዘመናት የነበረውን ጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ የቀየረና ኢትዮጵያን በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
ኢትዮጵያ “የዓባይ ውኃ የሁሉም ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ሀብት ነው” የሚለውን መርህ በተግባር በማስመስከር፣ የሕዳሴውን ግድብ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ የውኃ አጠቃቀም፣ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት በማያደርስና የትብብር መርሆዎችን ባከበረ መልኩ ገንብታዋለች።

ይህም የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚዋን ከማነቃቃት ባለፈ፣ በምሥራቅ አፍሪካ የቀጣናዊ የኃይል ትስስር ማዕከል በመሆን አዲስ የዲፕሎማሲ ዕድል ፈጥሮላታል።
ከዚህ ቀደም የግድቡ የድርድር ሂደት በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ለአፍሪካውያን ችግር የአፍሪካውያን መፍትሔ በሚለው መርህ እንዲመራ በማድረግ የተቋሙን አቅም ማሳየት የተቻለ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታም ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቷል።
ግድቡ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ያለምንም ወጪ ከከባድ የጎርፍ አደጋ የታደገ ሲሆን፣ ዓመቱን ሙሉ የተረጋጋ የውኃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ቀደም ሲል በበጋ ወቅት ይስተዋል የነበረውን የውኃ እጥረት አስቀርቷል።
ይህም ሀገራቱ የመስኖ ልማታቸውን እንዲያስፋፉ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ፣ ደለልን በመቀነስ ለእርሻ ሥራቸውና ለታችኞቹ ግድቦች ደኅንነት ከፍተኛ ጥቅም አበርክቷል።
ይህ እውነታ “ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ የውኃ እጥረት በመፍጠር ግብፅን ልትጎዳ ነው” የሚለው የዘመናት ፕሮፓጋንዳ በተግባር ሐሰት መሆኑን ያረጋገጠም ነው።

ሱዳን ግድቡ ጎርፍ በመቆጣጠር እና ደለልን በመቀነስ ረገድ ለእርሻዋና ለግድቦቿ ትልቅ ጥቅም እንዳለው የምታምን ቢሆንም፣ የግድቧን ደኅንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት እንዲኖር ፍላጎት አላት።
በሌላ በኩል ግብፅ የግድቡ መገንባት የውኃ ፍሰቴን ይቀንሰዋል በሚል ሥጋት፣ ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት ሳይፈረም የሚደረግ ማንኛውም እርምጃ ተቀባይነት የለውም የሚል አቋም በመያዝ የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ግብፅ አሁንም የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ተግባሯን የተወች አትመስልም፤ እውነታው ግን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሐሰት ስጋቶችን በተግባራዊ እውነታ ያፈረሰና የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ኘሮጀክት ነው፡፡
በበረከት ጌታቸው