AMN- ሰኔ 20/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያን ግብርና ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ሲፈትኑ ከነበሩት ማነቆዎች አንዱ የግብዓት በተለይም የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንደነበር ይነገራል፡፡
ለዚህም ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በ30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በቀጣዮቹ አምስት እና ስድስት ዓመታት ከሚተገበሩ ሰባት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አንዱ መሆኑን ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የዳንጎቴ ግሩፕ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ስምምነት ተፈራርመው በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ግንባታው ተጀምሯል፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም ማዳበሪያ አምራች ሀገራት አንዷ እንደሚያደርጋት ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ሲሆን፣ በቀጣይም ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግንባታ ሂደቱን በጎበኙበት ወቅት “በምግብ ራስን መቻል ዋነኛ አጀንዳችን ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
በምግብ ራስን ለመቻል መሬት ያስፈልጋል፣ ውኃ ያስፈልጋል፣ ሰው ያስፈልጋል፤ እነዚህ ደግሞ አሉን” በማለት የፋብሪካው መጠናቀቅ የሀገሪቱን ቁልፍ ችግር በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ በ”ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት፣ ሀገሪቱ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ለውጦችን በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነቷን እያረጋገጠች ነው፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያ የሚሆነው በበጋ እና በክረምት የስንዴ ልማት የተመዘገበው እመርታ ነው፡፡

በ2012 ዓ.ም የነበረው የመስኖ ስንዴ ልማት ከ20 ሺህ ሄክታር እና ከ600 ሺህ ኩንታል ምርት ብቻ የነበረ ሲሆን በ2017 ምርት ዘመን ወደ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር በማደግ ምርቱን 128 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በመኸር ወቅት የሚለማው ስንዴ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1.8 ሚሊዮን ሄክታር እና 53 ሚሊዮን ኩንታል ምርት፣ በ2017 ምርት ዘመን ወደ 4.3 ሚሊዮን ሄክታር እና 152 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ከፍ ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት 7.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ በመሸፈን 280 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ቀደም ሲል ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በመተካት ሀገሪቱ በየዓመቱ ታወጣ የነበረውን 1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር በሰብል ምርት ላይ ብቻ ሳይገደብ የኅብረተሰቡን የሥነ-ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ የተነደፈው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በተለይ በዶሮ፣ በወተት እና በእንቁላል ምርት ላይ አበረታች እድገት አስመዝግቧል፡፡
የሥነ-ምህዳር መታወክን ለመከላከልና ግብርናውን ዘላቂ ለማድረግ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እስከ አሁን 11.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡
ከተተከሉት ችግኞች መካከል 60 በመቶው ለጥምር እርሻ የሚውሉ በመሆናቸው ከተፈጥሮ ጥበቃ ባለፈ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ አውሎ በስፋት ወደ ውጭ መላክ ተችሏል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (ኤ አይ) በስፋት እየታገዘ መምጣቱ ምርታማ፣ በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውሶችን የመቋቋም አቅሙ የዳበረ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህም ዘርፉ ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በጎዴ እየተገነባ ያለው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ለአርሶ አደሩ ዋነኛ የድጋፍ ምሰሶ በመሆን የስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት እና የጥምር እርሻ እና ሌሎች ስኬቶች ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” በሚለው ሀገራዊ መርህ ስር እየተመዘገቡ ያሉት ተጨባጭ የግብርና ውጤቶች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ እያፋጠኑ መሆኑን በዘርፉ የተገኙ ውጤቶች ያመላክታሉ፡፡
በትዝታ መንግስቱ