ኢትዮጵያውያን ለዛሬ ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር ጥራት ያለው ሥራ ሊሰሩ ይገባል — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያውያን ለዛሬ ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር ጥራት ያለው ሥራ ሊሰሩ ይገባል — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN — ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ማናቸውም የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለዕለት ፍጆታ የሚሆኑ ሳይሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሸጋገሩና ዘላቂ አሻራ የሚያኖሩ መሆን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ከተማ የተገነቡ ግዙፍ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ላይ የሚያከናውነው ሥራ በእሱ ዕድሜ የሚፈርስ መሆን የለበትም ብለዋል።

“የለብለብ ሥራ ወይም የዛሬ ማትረፍ ሥራ ብቻ መሆን የለበትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እያንዳንዱ ግንባታ ጥራቱን የጠበቀ፣ የአካባቢውን ባህልና ሥነ-ልቦና የሚገልጽ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ በግሉ ዘርፍ የተከናወነውን የኩሪፍቱ ሪዞርት ግንባታን እንደ አርአያ በመጥቀስ፣ ሥራው ጥራት ያለውና ለአርባ ምንጭ ሕዝብ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ክብር የሰጠ በመሆኑ ለትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰው በሀገሩ የሚገነባው የግንባታ ሥራ የሚዘልቅ፣ የሚሻገር፣ የሚወረስ እና ልጆቻችን የአባቶቻቸውን ስም በጥሩ ሥራቸው እያነሱ የሚያተርፉበት ሥራ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የግሉ ሴክተርም ሆነ ሌሎች አልሚዎች ይህንን የጥራትና የዘላቂነት ፈለግ ተከተለው እንዲሠሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review