AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም


የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና ልዑካኖቻቸዉን አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት ተቀብለዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተውንና እያደገ የመጣውን የአፍሪካ-ሩሲያ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር መክረዋል፡፡
መሪዎቹ አጀንዳ 2063ን ጨምሮ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን ለመደገፍ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምግብ ዋስትና፣ በሕዝብ ጤና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች ያለውን ትብብር ማሳደግ በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል፡፡

ሊቀመንበሩ፤ ሩሲያ በመላው አፍሪካ እያደረገች ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድገት ያደነቁ ሲሆን፣ በሰብአዊ እርዳታ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በምግብ ዋስትና እና በአቅም ግንባታ ዘርፎች የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በበጎነት ተቀብለዋል።
የሩሲያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ዉስጥ ቋሚ የአፍሪካ ውክልና እንዲኖራት የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያደነቁት ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ የግብርና ምርቶች እና የማዕድን ሀብቶች ላይ እሴት መጨመርን በተመለከተ በሊቀመንበሩ የቀረበውን ጥሪ ደግፈዋል።
እንዲሁም እንደ አፍሪካ ሰብአዊ ኤጀንሲ እና አፍሪካ የመድኃኒት ኤጀንሲ ያሉትን የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ መዋቅሮች ለማጠናከር ሩሲያ የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ እና ሚኒስትር ላቭሮቭ የአፍሪካ ህብረት እና ሩሲያ ስልታዊ አጋርነትን ለማስቀጠል እና 3ኛውን የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸዉን ከኮሚሽኑ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ