AMN-ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የሚገቡ ቀሪ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የሚለዩ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ።
እስካሁን በተደረጉ የ16ቱ ዙር የጥሎማለፍ ጨዋታዎች ሞሮኮ ፣ ፈረንሳይ ፣ ኖርዌይ ፣ እንግሊዝ ፣ ስፔን እና ቤልጂየም ሩብ ፍፃሜ የገቡ ሀገራት ሆነዋል። ዛሬ ደግሞ አርጀንቲና ከ ግብፅ ፤ ስዊዘርላንድ ከ ኮሎምቢያ ይጫወታሉ።
አርጀንቲና ከ ግብፅ

በኬፕ ቨርዴ ያልተጠበቀ ፈተና ገጥሟት 3ለ2 አሸንፋ ያለፈችው አርጀንቲና ዛሬም ሌላኛዋን አፍሪካዊት ሀገር ትፋለማለች። የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና አሁንም 39 ዓመት በሞላው ኮከቧ ሊዮኔል ሜሲ ላይ ጥገኛ ናት።

የኳታሩን የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና እንድታሸንፍ የሜሲ ሰባት ግቦች የገዘፈ አስተዋፅኦ ነበራቸው ፤ ዘንድሮም ልዩነት ፈጣሪነቱን የቀጠለው የኢንተር ሚያሚው ተጫዋች ገና በአራት ጨዋታ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል።
ሜሲ በግሉም በውድድሩ ታሪክ ለማሻሻል የሚከብዱ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ ይገኛል። በኬፕ ቨርዴው ጨዋታ 120 ደቂቃ የተጫወተው የቀድሞ የባርሰሎና ታሪካዊ ተጫዋች በዛሬውም ጨዋታ የሊዮኔል ስካሎኒ መተማመኛ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አውስትራሊያን በመለያ ምት ያሸነፈችው ግብፅ በውድድሩ ተጨማሪ ታሪክ ለመፃፍ ተዘጋጅታለች። በዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል ቀዳሚ የሆነችው ሀገር ለዚህ ጥሎ ማለፍ ስትደርስ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ዛሬ ድል ከቀናት ከካሜሩን ፣ ሴኔጋል ፣ ጋና እና ሞሮኮ በመቀጠል ሩብ ፍፃሜ የገባች አምስተኛዋ አፍሪካዊ ሀገር ትሆናለች። ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ይህን አዲስ ታሪክ ለመስራት የአምበሏ ሞሐመድ ሳላህን ብቃት ትፈልጋለች።
የቀድሞ የሊቨርፑል ተጫዋች አንድ ግብ ብቻ ቢያስቆጥርም የማጥቃቱ ሂደት ሃይል እርሱ ነው። ሳላህ በዘንድሮ ውድድር በአጠቃላይ 16 የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የብሔራዊ ቡድኑ የልብ ትርታ መሆኑን አስመስክሯል።
አርጀንቲና እና ግብፅ እኤአ በ2008 በካይሮ ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ብቸኛ ግንኙነታቸው ነው። ግጥሚያውን አርጀንቲና 2ለ0 ማሸነፍ ችላ ነበር።
በአትላንታ ስታዲየም የሚከናወነው የሁለቱ ሀገራት የዛሬ ፍልሚያ ምሽት 1፡00 ይጀምራል።
ስዊዘርላንድ ከ ኮሎምቢያ
ብዙም ሳይጠበቁ እዚህ የደረሱት ስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ ከዚህ ቀደም የሰሩትን ታሪክ ለመጋራት ይፋለማሉ። ሁለቱ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ትልቁ ውጤታቸው ሩብ ፍፃሜ መድረስ ነው። ዛሬ የሚያሸንፍ ሀገር ይህን ታሪኩን የሚደግም ይሆናል።
በ32ቱ የጥሎማለፍ ዙር ኮሎምቢያ ጋናን 1ለ0 በማሸነፍ ፤ ስዊዘርላንድ ደግሞ ሌላኛዋን አፍሪካዊ ሀገር አልጄሪያን 2ለ0 በመርታት ነው ለዛሬ ጨዋታ የበቁት።
ስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው። ከዚህ ቀደም እኤአ 1994 ላይ በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ ተደልድለው ኮሎምቢያ 2ለ0 አሸንፋ ነበር።
በካናዳ ቫንኩቨር ቢሲ ፓላስ ስታዲየም የሚከናወነው የሁለቱ ሀገራት ዛሬ ግጥሚያ ምሽት 5፡00 ይጀምራል።
በሸዋንግዛው ግርማ S
See less