AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ክፍለ ኢኮኖሚ ታሪካዊ ሊባል የሚችል መዋቅራዊ ሽግግርና አመርቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ፣ ከለውጡ በፊት ከ47 በመቶ በታች የነበረው የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት ወደ 67 በመቶ ከፍ ሊል ችሏል።

ይህ ትልቅ እምርታ ሰፊ የሥራ ዕድል፣ የነቃ የንግድ እንቅስቃሴና ሀብት እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የ24 በመቶ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ የ20 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣዩ ዓመት ከኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከውጭ የምታስገባቸውን የኢንዱስትሪ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት በመተካት በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ፈጽሞ የማታውቀውን የሶላር ምርቶች ኤክስፖርት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጀመር መቻሏ የዘርፉን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢኮኖሚ ለውጥ ሂደቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን የመቋቋም እና እንቅፋቶችን ወደ መልካም ዕድል የመቀየር መርሆዎችን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በበረከት ጌታቸው