AMN- ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን፣ የተመዘገቡ ስኬቶችን እና መፍትሔ የሚሹ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት በሁሉም ክልሎች ሞዴል እና “ቦርዲንግ” ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም የተጎዱ ተቋማትን በመጠገን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የትምህርት ተቋማት ግንባታዎች የትምህርት ጥራትን ከመጠበቅ ይልቅ በመጠን ላይ ያተኮሩ እንደነበሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ የወደፊት የዓለም ተስፋ መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት ቀድሞ በመዘጋጀት ዘርፉን ወደ ሥራ ማስገባቱንም አብራርተዋል።
እስካሁን በተገኘው ውጤት መሠረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አንስተዋል።

ተማሪዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የመምህራን ሚና ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በትምህርት ዘርፉ የታዩትን ስብራቶች ለመጠገን እና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ጊዜ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።

በትምህርት ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የተሟሉ ባይሆኑም በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች በመለየትና የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ
See less