“መንገድ ሰርተን ሌላውን መተው አንችልም” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሃምሌ 1/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎትን ለማሟላት ቢያንስ ሁለት ትሪሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለተነሱላቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገሪቱ ካላት ጠቅላላ በጀት ጋር የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎትን ማነጻጸር እንደሚገባ በመጠቆም፣ በሚመደበዉ በጀት የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎትን መሸፈን እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

መንገድ ሰርተን ሌላውን መተው አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት መለየት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ማነቆዎችን ሲያብራሩም ፤ በካሳ አሰጣጥ ዙሪያ ከቀበሌ እና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከነጋዴዎች ጋር በተያያዘ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ችግሮች ለፕሮጀክቶች መጓተት ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የገንዘብ ምንጩ ሳይታወቅ ፕሮጀክቶችን ማወጅ እና በጀት ሳይያዝ ሥራ መጀመር ለችግሩ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት ቀጣይ ትኩረት፣ አቅምን መሰረት በማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፕሮጀክቶች መለየት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በየመንገዱ አዳዲስ ቃል ከመግባት ይልቅ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚገኙ የመንገድ ሥራዎች ላይ የአመራር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየደረጃው ያሉ አካላት በተግባር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን በቅርበት መከታተል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የአሁኑ ዘመን የመንገድ ሥራ ክትትልና አፈጻጸም በኢትዮጵያ ታሪክ ከተደረጉት የተሻለ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት ክትትል (Remote Monitoring) እየተደረገ በመሆኑ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አንስተዋል።

እንደ ደባርቅ-ጎንደር እና ባሌ ያሉ አካባቢዎችን እንደ ማሳያ በመጥቀስ፣ ችግሮች ቢኖሩም ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review