AMN- ሐምሌ 1/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የራሷን የኢኮኖሚ፣ የጤና እና የሰላም መሠረት በማጠናከር ወደፊት ራሷን ችላ ለሌሎች የምትተርፍ ጠንካራ ሀገር የመሆን ጉዞዋን እያጠናከረች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የወደቁትን ታነሳለች፤ የተኙትንም ታነቃለች፤ ወደ ብልጽግና ጉዞም ትወስዳቸዋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ የምትችለው ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመተግበር የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ ግብርና እና ቱሪዝምን ማነቃቃት፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታት እና እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በስኬት እያከናዎነች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራዋ አስገብታለች፤ የግብርና ዘርፉም 7.7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።
የቱሪዝም የስበት ማዕከል እየሆነች ያለቸው ኢትዮጵያ፣ ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን አስተናግዳለች፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 21 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ባጠቃላይ 9.8 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል።
ከውጭ የምታስገባቸውን የኢንዱስትሪ ምርቶች በአገር ውስጥ በመተካት በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ ማዳን የቻለች ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት ከኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘትም አቅዳለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት 1.2 ሚሊዮን ቤቶች የተገነባላት ኢትዮጵያ በቀጣይ 1.5 ሚሊዮን ተጨማሪ ቤቶች ሊገነቡ ውጥን ተይዟል፡፡
የኢኮኖሚ ለውጡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን የሚቋቋም እና እንቅፋቶችን ወደ መልካም ዕድል የመቀየር አቅም ማጎልበቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
በታደሠ ሽፈራው