በአዲስ አበባ የከባድ ወንጀል ምጣኔ በ47 በመቶ ቀንሷል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በአዲስ አበባ የከባድ ወንጀል ምጣኔ በ47 በመቶ ቀንሷል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ካለፈው ዓመት አንጻር ሲነጻጸር ዘንድሮ የከባድ ወንጀል ምጣኔ ከ47 በመቶ በላይ መቀነሱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤት አባላት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ የከተማዋን የሕግ ማዕቀፍ ወቅቱን የዋጀ ለማድረግ 85 ደንቦች እና 19 አዋጆች ተሻሽለውና አዲስ ወጥተው በካቢኔና በምክር ቤት መጽደቃቸውን አንስተዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የፍትሐብሔር ጉዳዮች የፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎ ውሳኔ ያረፈባቸው 16 ሺህ 874 መዝገቦች ውስጥ 15 ሺህ 836 መዝገቦች ለከተማ አሥተዳደሩ በማስወሰን ከ21 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የሕዝብና የመንግሥት መብትና ጥቅም ማስከበር መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም በወንጀል ሕግ የምርመራ መዝገብ የቀረቡ 64 ሺህ 500 የወንጀል መዛግብት በመመርመር የማጥራት ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ምርመራቸው ከተጠናቀቁ 50 ሺህ 874 የግል አቤቱታ የወንጀል መዝገቦች 87 ነጥብ 2 በመቶ በዕርቅ ለመጨረስ ታቅዶ፤ 44 ሺህ 260 መዛግብት በዕርቅ መዘጋቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ በ15 ሺህ 545 የወንጀል መዝገቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ መወሰኑን አመላክተዋል፡፡

የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ከማስፈጸምን አንጻር ደግሞ ከ1 ሺህ 690 ጉዳዮች መካከል፤ በ1 ሺህ 686 መዝገቦች ላይ ማስፈጸም መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በትዝታ መንግሥቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review