ጭፍራና የአካባቢው የማህበረሰብ ሬዲዮ ፈቃድ አገኘ

AMN ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአፋር ክልል፣ አውሲ ረሱ ዞን ጭፍራ ወረዳ ለሚገኘው ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ሰጠ።

የፈቃድ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ፣ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሬዲዮዎች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ኢስማኤል ጡኃ እንዲሁም የጭፍራ ወረዳ አስተዳዳሪና የሬዲዮ ጣቢያው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ አርቦ በተገኙበት ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ በፈቃድ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራችን በአሁኑ ወቅት 52 የማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስደው የማህበረሰቡን የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ እና የመልካም አስተዳደር ክንውኖችን መሰረት አድርገው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ፣ ባህልን የሚያሳድጉ እና በነዋሪዎች መካከል የጋራ መግባባትና በጎ ስነ-ምግባር የሚያጠናክሩ ፕሮግራሞችን ቅድሚያ ሰጥተው መስራታቸውን አሁንም አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዛሬው እለት በአዲስ ተመዝግቦ ፈቃድ የወሰደው የጭፍራ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያም ይህን የኃላፊነት ስሜት በመላበስ ለወረዳው ህዝብ የልማትና የመረጃ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል መልእክት አስተላልፈዋል።

የጭፍራ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የሬዲዮ ጣቢያው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ አርቦ በበኩላቸው፣ የሬዲዮ ጣቢያው መቋቋም ለወረዳው ነዋሪዎች ዘመናዊ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

አያይዘውም ጣቢያው የልማት ሥራዎችን በስፋት በማስተዋወቅ፣ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በቅርበት በመከታተል እና ምላሽ በመስጠት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በ2018 በጀት ዓመት ለሁለት አዳዲስ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ ለ52 ነባር የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃንም የፈቃድ ዕድሳት ማከናወኑን ከባለሥልጣኑ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review