“ደጋፊዎች የሚኮሩበት ቡድን መስራት እፈልጋለሁ” አንዶኒ ኢራዮላ

AMN-ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

አዲሱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራዮላ ደጋፊዎችን የሚያኮራ ቡድን መስራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

የ44 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ ቀዮቹን ከተረከበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

“ሊቨርፑል ግዙፍ ክለብ እንደሆነ አውቃለሁ ፤ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ዝግጁ ነኝ።” ብሏል።

“አሁን ለምናገራቸው ነገሮች መጠንቀቅ እንዳለብኝ አውቃለሁ ፣ ነገር ግን ደጋፊዎች ይሄ የኔ ቡድን ነው ብለው የሚደሰቱበት እና በቀላሉ የሚለዩት ቡድን መስራት እፈልጋለሁ” ሲል መስራት ስለሚፈልገው ቡድን አብራርቷል።

የሁለት ዓመት ውል ብቻ ስለመፈረሙ የተጠየቀው የቀድሞ የቦርንማውዝ አሰልጣኝ “ለአሰልጣኝ የውል ርዝማኔ ረብ የለሽ ነው፤ ውል ስላለኝ የምቆይ መሆን አልፈልግም” ብሏል።

ከዝውውር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ ሊመጡ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥቷል።

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው የመርሲሳይዱ ክለብ ቀጣይ ሳምንት ሰኞ ወደ አሜሪካ ያቀናል።

በቆይታውም ከሰንደርላንድ ፣ ሬክሳም እና ሊድስ ዩናይትድ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያከናውናል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review