AMN- ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

ብሔራዊ የታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይል በ2018 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ እና የሪፎርም ስራዎች አፈፃፀም እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል።

ግብረ-ኃይሉ በገቢ አስተዳደር ተግባራት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ የታክስ እና ጉምሩክ ፖሊሲዎች ፣ የገቢ ዘርፍ ሪፎርም ሥራዎች፤ የሀገር ውስጥ ታክስ እንዲሁም የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ አስተዳደር ተግባራት ዙሪያ በዝርዝር መክሯል።
በ2018 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ታክስ እና የጉምሩክ ቀረጥ አሰባሰብ ከተያዘው ግብ አንፃር ከዕቅድ በላይ መፈጸም ስለመቻሉ ግብረ-ኃይሉ መገምገሙን ነው የተገለጸው፡፡

ለስኬቱም የማክሮ ኢኮኖሚ እና የገቢው ዘርፍ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች ፣ ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ያለው የሰራ ትብብር፣ ለገቢው ዘርፍ ሰራተኞች የተደረገው የማትጊያ እና የታየው ውጤታማ የሥራ አመራር እንዲሁም የገቢው ዘርፍ ሪፎርም ተግባራት በአግባቡ መከናወናቸው ውጤቱ እንዲመዘገብ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ተብሏል።

በተያዘው 2019 በጀት ዓመትም በተቋማቱ የተጠናከረ የሥራ አመራር ተግባራት እንደሚከናወኑ እንዲሁም ብሔራዊ የታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይል የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደርግ መገለጹን ከገቢዮች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የብሔራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም ከጉምሩክ ኮሚሽን በተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ነው።