AMN – ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በምትገነባበት ወቅት ተደብቀው የሚያደፍጡ፣ ነገር ግን በውስጥ ልዩነቶች ምክንያት ስትጨቃጨቅ ዕድልና ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ የሚገቡና ሽብልቅ በመክተት መሻቶቿ እንዳይሳኩ የሚያደርጉ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ታሪክ ከጉንደት እስከ ጉራዕ፣ ከአድዋ እስከ ማይጨው፣ እንዲሁም ከካራማራ እስከ ባድመ ድረስ ያለውን ሂደት ብንመረምር በእነዚህ ሁሉ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና መሻት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ያስተዳደረችውን፣ በባለቤትነት የያዘችውን፣ ለራሷም ለአካባቢውም መጠቀሚያ ያኖረችውን ቀይ ባሕር ያልተመረጠ መንግሥት፣ ያልተወያየ መንግሥት በሸፍጥ ኢትዮጵያን የጂኦግራፊ እስረኛ ያደረገበት ዋናው ምክንያት በውስጥ ያለን ስንፍና እንጂ የኢትዮጵያን መሻትና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል ስለነበረ አይደለም ብለዋል።

ልማት ሲጀመር፣ ከተሞች ሲገነቡና ህዳሴ ሲታለም አብረው የሌሉ ኃይሎች፣ በሀገር ውስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ግን ጥይት፣ ገንዘብና የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ በማቅረብ ጣልቃ እንደሚገቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

እነዚህን ኃይሎች በአሞራዎች የመሰሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አሞራ ሲታረድ እንጂ ሲገነባ እንደማይመጣም ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የትኛውም ዓይነት የውስጥ ልዩነትና አለመግባባት በውይይትና በንግግር ሊፈታ እንደሚችል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎትና መሻት ለሌሎች ኃይሎች ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥና በታሪክ ውስጥ እንደ እንክርዳድ የሚቆጠር ዜጋ እንዳይኖር፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት እንዲያደርግም አሳስበዋል።
በታደሠ ሽፈራው