የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂክ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ ነው

AMN- ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂክ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም በአውሮፓ ሕብረትና በአፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ላይ በመምከር፣ በጋራ ጥቅሞችና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

በተጨማሪም በቀጣናዊ እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ተመስርተው ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ይበልጥ ለማሳደግና ለማስፋፋት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ መክረዋል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን የዘመናት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር፣ እንዲሁም በጋራ ጥቅም እና በአጋርነት ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ሕብረቱ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ግብዓቶች የተገኙበት ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር የነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያንና የሕብረቱን አጋርነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የሚኖረውን የኢንቨስትመንት፣ የዲጂታል አስተዳደር፣ የታዳሽ ኃይል እና የሌሎች ዘርፎች ትብብር የበለጠ ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ፍላጎት እያደገ መምጣቱም የንግድ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግና ሥራዎቻቸውን ለማስፋፋት ትልቅ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ዕድልም ለሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነት ለማዋል እንደሚሰራ ተገልጿል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት በዲጂታል አስተዳደር ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ አመላክተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ በመስራት ለጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ አብራርተዋል።

ሕብረቱ በአገሪቱ የጥሬ ዕቃዎች ላይ እሴት መጨመርን በመደገፍ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲስፋፋ እንደሚያግዝ ያረጋገጡ ሲሆን ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራ መስፋፋት የሚኖረውን ወሳኝ ሚና ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review