ከእግርኳስ በላይ የሆነው የእርስ በእርስ ግንኙነት

AMN- ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

እንግሊዝ በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚገኘው የፎክላንድ ደሴቶች የግሏ እንደሆነ ለዓለም ስትነግር ከርማለች። እ.አ.አ በ1774 ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጿን አሰማች ፤ በ1832 ደግማ እወቁልኝ አለች።

ግዛቴ ያለችው የፎክላንድ ደሴቶች ግን በ1982 በአርጀንቲና ወታደሮች ተወረራባት። ግዛቴን ለቃቹህ ውጡ የሚል መልዕክት ብታስተላልፍም ሰሚ አጣች።

አርጀንቲናውያን “ላስ ማልቪናስ” እያሉ የሚጠሩትን የፎክላንድ ደሴቶች የግላችን ነው አሉ። በወቅቱ ደቡብ አሜሪካዊቷን ሀገር በፕሬዝዳንትነት ይመሩ የነበሩት ጀነራል ሎኦፖልዶ ጋልቲኤሪ ለጉዳዩ ቆራጥ አቋም መያዛቸውን አሳወቁ።

እንግሊዝ ግዛቴ ያለችውን የፎክላንድ ደሴቶችን ለማስለቀቅ ወደ ጦርነት ገባች። 74 ቀናት በፈጀው ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች 907 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። አርጀንቲና በጦርነቱ ተሸንፋ እጅ ሰጠች። እንግሊዝም ዳግም የፎክላንድ ደሴቶችን በቁጥጥሯ ስር አስገባች።

ይህ ታሪክ ለአርጀንቲናውያን ቅስም ሰባሪ ሆኖ አልፏል። ባገኙት አጋጣሚ ይህን ቁስል የሚሽርላቸው ነገር ይፈልጋሉ። ለዚህ እንደ አንድ አማራጭ የሚወስዱት እግርኳስን ነው።

እንግሊዝ እና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫው አምስት ጊዜ ተገናኝተዋል። የትኛውም የ1986ቱን ያህል ለዘመናት በእዝነ ህሊና የሚቆይ ትውስታ የሰጠ ጨዋታ የለም።

ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና እና የቡድን አጋሮቹ የሀገሪቱ መሪዎች በሰጡት ቃል መሰረት የፎክላንድ ደሴቶች ጦርነትን እንዳሸነፉ ነበር የሚያውቁት። የ1982ቱን የዓለም ዋንጫ ለመካፈል ወደ ስፔን ባቀኑበት ወቅት ግን እውነታውን አወቁ።

በሰሙት መረጃ ቢበግኑም እንግሊዝን ሚበቀሉበት ዕድል ግን አላገኙም። በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ምድባቸውን እንኳን ማለፍ ተስኗቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

በ1986 ግን ሲመኙት የከረሙት ጊዜ መጣ ፤ የዋንጫ ባለቤት ሆነው ባጠናቀቁበት የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ላይ እንግሊዝን በሩብ ፍፃሜ አገኙ።

ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና እና አጋሮቹ በፎክለንድ ደሴቶች የተቀጠፉ ዜጎቻቸውን በማሰብ ጨዋታውን ለማሸነፍ ተነሳሱ። በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ሁለት ግቦች ታግዛ አርጀንቲና 2ለ1 አሸነፈች።

ጨዋታው ከተከናወነ 40 ዓመታት ቢሞላም አርጀንቲናውያን ሁለቱን ግቦች ደግመው ደጋግመው ተመልክተውታል። የማራዶና የመጀመሪያ ግብ “የፈጣሪ እጅ” የሚል ስያሜ የሰጣት በግልፅ በእጅ የተቆጠረች ናት።

ፊፋ የጨዋታውን ክብደት በማየት ገለልተኛ ይሆናሉ ብሎ የመደባቸው ቱኒዚያዊው ዋና ዳኛ አሊ ቤን ናስር ግን ሳይመለከቱት ቀርተዋል። ሁለተኛው ግን “የምዕተ ዓመቱ ምርጥ” የተባለለት ስድስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አልፎ ያስቆጠረው ድንቅ ግብ ነው።

ከድሉ በኋላ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና “በጦርነቱ እንደ ትናንሽ ወፎች እየተለቀሙ ለተገደሉት አርጀንቲናውያን ወጣቶች በቀል ነው” ሲል ተናገረ።

ከዚህ ክስተት በኋላ ነው አርጀንቲናውያን ከስድስት ዓመት በፊት ሕይወቱን ያጣው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶናን ከማንም ጋር ማነፃፀር የማይፈልጉት።

እንግሊዝ እና አርጀንቲና ከዚህ በውዝግብ ከተሞላ ጨዋታ በፊት በ1962 እና 1966 የዓለም ዋንጫ ላይ ተገናኝተው ነበር። በሁለቱም አጋጣሚ እንግሊዝ ማሸነፍ ችላለች።

በተለይ በ1966 እንግሊዝ ያዘጋጀችውን የዓለም ዋንጫ በሀገሯ ስታስቀር በሩብ ፍፃሜ የገጠመችው አርጀንቲናን ነበር። እንግሊዝ ጨዋታውን 1ለ0 ካሸነፈች በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አልፍ ራምሴ የአርጀንቲናውያን ሃይል የቀላቀለበት ጨዋታ ተችተው ተጫዋቾቹን “እንስሳ” በማለት ገልፀው ነበር። ንግግሩ አርጀንቲናውያንን አስቆጥቶ ነበር።

ሌላው የውዝግብ ታሪክ የነበረው የእንግሊዝ እና አርጀንቲና ጨዋታ በ1998ቱ የፈረንሳዩ የዓለም ዋንጫ ላይ በ16ቱ ጥሎማለፍ ያደረጉት ነው። ዴቪድ ቤክሃም በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ በወጣበት ጨዋታ አርጀንቲና በመለያ ምት አሸንፋ አልፋለች።

የሁለቱ ሀገራት የመጨረሻ ግንኙነት በ2002 በምድብ ያደረጉት ሲሆን እንግሊዝ በዴቪድ ቤክሃም የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1ለ0 አሸንፋለች።

እንግሊዝ በአጠቃላይ ከአምስቱ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ሦስቱን በድል ተወጥታለች። አርጀንቲና ደግሞ ሁለቱን ማሸነፍ ችላለች።

ዛሬ ለስድስተኛ ጊዜ የሚያደርጉት ጨዋታስ ምን ዓይነት ውጤት ይመዘገብብት ይሆን?

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review