AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት እና የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አፈፃፀም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት እና ከሀገር ውጭ ያሉ ገበያዎችን ለመቀላቀል አልሞ ባቀደው የሦስት ዓመት የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አማካኝነት በ2018 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 215 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ33 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።
ተቋሙ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 90 ነጥብ 1 ሚሊዮን በማሳደግ የዕቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ያሳካ ሲሆን ፣ 195 አዳዲስ አገልግሎቶችን አስተዋውቆ አጠቃላይ የአገልግሎቶቹን ብዛት ወደ 475 አድርሷል።
ለአስተማማኝ መሠረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ 75.66 ቢሊዮን ብር ወጪ ያደረገው ተቋሙ ፣ 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን በመገንባት ጠቅላላ ጣቢያዎችን 1 ሺህ 613 አድርሷል ብለዋል።
ተጨማሪ 264 ከተሞችን የ4ጂ ተጠቃሚ በማድረግ አጠቃላይ የ4ጂ ተደራሽነቱን ወደ 1 ሺህ 200 ከተሞች (82.2 በመቶ) ያሳደገ ሲሆን፣ የ5ጂ አውታረ መረቡንም በ33 ከተሞች ማዳረሱን ነው ያብራሩት።
195 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎችን የኔትዎርክ ተጠቃሚ ያደረገው ተቋሙ ተጨማሪ 10.2 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል መሠረተ ልማት ስለመገንባቱም አንስተዋል።
በዲጂታል ፋይናንስ እና አገልግሎት ዘርፍ፣ የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 60.59 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በቀን በአማካይ 11 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተካሂዶበታል ሲሉ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራም 19 ነጥብ 72 ሚሊዮን ደንበኞች የዲጂታል ብድር አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።
ከዚህ ባለፈም ተቋሙ በዘመን ገበያ 21ነጥብ 7 ሚሊዮን የዲጂታል ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን ፣ በሀገራችን 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ስለማካሄዱ ተናግረዋል።
በሄለን ጀምበሬ