AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አህመድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤትን ጎበኘ።
የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በቆይታቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስላላት የጎላ ሚና አብራርተዋል።
አቶ ባሕሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) እና የአፍሪካ ዋንጫን ከመመስረት ጀምሮ፣ ውድድሩን በማስተናገድ እና ዋንጫውን በማንሳት ረገድ የነበራትን ታሪካዊ አሻራ አውስተዋል።

በውይይቱ የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ችግር እንደሌለ ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አሊ አህመድ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን የሚጫወት በመሆኑ ለኢትዮጵያ የመጫወት ዕድሉ ባይገጥመውም፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በማስተባበርና በማነሳሳት በፌዴሬሽኑ የዲያስፖራ ኢንተግሬሽን ፕሮግራም ላይ የጎላ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበውለታል።

አሊ አህመድ በበኩሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ መሆኑን ገልጾ፣ በርካታ ባለተሰጥኦ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በውጭ ሀገራት እንደሚገኙ ጠቁሟል።
አክሎም ከፌዴሬሽኑ ጋር በዲያስፖራ ኢንተግሬሽን ፕሮግራሙ ላይ አብሮ ለመሥራትና የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።