ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215.8 ቢሊዮን ገቢ አገኘ

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

‎የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።

‎ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት እና የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አፈፃፀም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

‎ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት እና ከሀገር ውጭ ያሉ ገበያዎችን ለመቀላቀል አልሞ ባቀደው የሦስት ዓመት የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አማካኝነት በ2018 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።

‎በበጀት ዓመቱ 215 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ33 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።

‎ተቋሙ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 90 ነጥብ 1 ሚሊዮን በማሳደግ የዕቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ያሳካ ሲሆን ፣ 195 አዳዲስ አገልግሎቶችን አስተዋውቆ አጠቃላይ የአገልግሎቶቹን ብዛት ወደ 475 አድርሷል።

‎ለአስተማማኝ መሠረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ 75.66 ቢሊዮን ብር ወጪ ያደረገው ተቋሙ ፣ 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን በመገንባት ጠቅላላ ጣቢያዎችን 1 ሺህ 613 አድርሷል ብለዋል።

‎ተጨማሪ 264 ከተሞችን የ4ጂ ተጠቃሚ በማድረግ አጠቃላይ የ4ጂ ተደራሽነቱን ወደ 1 ሺህ 200 ከተሞች (82.2 በመቶ) ያሳደገ ሲሆን፣ የ5ጂ አውታረ መረቡንም በ33 ከተሞች ማዳረሱን ነው ያብራሩት።

‎195 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎችን የኔትዎርክ ተጠቃሚ ያደረገው ተቋሙ ተጨማሪ 10.2 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል መሠረተ ልማት ስለመገንባቱም አንስተዋል።

‎በዲጂታል ፋይናንስ እና አገልግሎት ዘርፍ፣ የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 60.59 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በቀን በአማካይ 11 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተካሂዶበታል ሲሉ ገልጸዋል።

‎የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራም 19 ነጥብ 72 ሚሊዮን ደንበኞች የዲጂታል ብድር አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።

‎ከዚህ ባለፈም ተቋሙ በዘመን ገበያ 21ነጥብ 7 ሚሊዮን የዲጂታል ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን ፣ በሀገራችን 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ስለማካሄዱ ተናግረዋል።

በሄለን ጀምበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review