በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ላይ ተሳትፈዉ በተገኙ 5 ሺህ 857 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል

You are currently viewing በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ላይ ተሳትፈዉ በተገኙ 5 ሺህ 857 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል

AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

ሌብነትን፣ ዳተኝነትን እና የህዝብ እንግልትን በማስወገድ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥርዓት ለማስፈን በተወሰደ እርምጃ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 5 ሺህ 857 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተገልጋዮች ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ሪፓርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ፤ አገልግሎት አሰጣጥን ግልፅና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ፣ አስተዳደሩ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (AMN) በኩል አዳዲስ አሰራሮችን ዘርግቷል።

እነዚህም “አገልጋዩ” ፕሮግራም አመራሩ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቀጥታ ስርጭት ምላሽ የሚሰጥበት እንዲሁም “ዋርካ” ፕሮግራም አገልጋዩ እና ሕዝቡ በአካል ተገናኝተው ፊት ለፊት የሚጠያየቁበት የውይይት መድረኮች ናቸው።

በእነዚህ የሚዲያ መድረኮች ከተነሱት የተገልጋይ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት አፋጣኝ ምላሽ አግኝተው መፈታታቸው ከንቲባዋ አመላክተዋል።

ይህ አሰራር በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሥር ሰዶ የቆየውን ዳተኝነት በመቅረፍ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት በፈጠሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ አስችሏል ብለዋል።

ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በተጨባጭ ለመታገል በተያዘው ቁርጠኛ አቋም፣ በጥፋት ላይ ተሰማርተው በተገኙ 5 ሺህ 857 አካላት ላይ እንደ ጥፋታቸው ክብደት ከማስጠንቀቂያ እስከ ስንብት እና በህግ ተጠያቂ ማድረግ የሚደርሱ እርምጃዎች ተወስደዋል።

እነዚህም 79 ሹመኛ አመራሮች ፣ 213 ዳይሬክተሮች እና የቡድን መሪዎች፣ 5 ሺህ 430 ባለሙያዎች እንዲሁም 135 ተገልጋዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ጥፋተኞችን ከመቅጣት ጎን ለጎን፣ የመንግስት ሰራተኛውን የኑሮ ጫና ከግንዛቤ ያስገቡ ማበረታቻዎችን በተግባር አውሏል። ከንቲባዋ በሪፖርታቸው እንዳብራሩት ለሰራተኛው ሁለት ጊዜ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጓል።

በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በመመደብ የሰራተኞች ካፍቴሪያ በድጐማ እንዲቀርብ ከመደረጉም በላይ፣ በየተቋማቱ የሸማቾች ሱቆች ተደራጅተዋል።

በተጨማሪ ሴት ሰራተኞች ያለ ስጋት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በየተቋማቱ የህፃናት ማቆያዎች ከነሙሉ ወጪያቸው ተደራጅተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህ ተጠያቂነትን የማስፈን እና ሰራተኛውን የመደገፍ የተቀናጁ ስራዎች የመንግሥት ተቋማትን ብቃት እና አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋገሩ ውጤቶች ሆነው መመዝገባቸው በሪፓርቱ ተገልጿል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review