በከተማዋ የሚሰጡ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች የተቀናጁ በመሆናቸው ስኬታማ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል

AMN – ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

በከተማዋ የሚሰጡ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች የተቀናጁ እና ተናባቢ እንዲሆኑ ማድረግ በመቻሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስኬታማ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ተናገሩ።

አዲስ አበባ ለወጠነችው ሁለንተናዊ የብልፅግና ተምሳሌታዊ ግብ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ስሉጥ ማድረግ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህን ተልዕኮ እየተወጣ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የሴክተር ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ጨምሮ የዘርፉ የአምስት ዓመት ሪፖርት፣ እንዲሁም የትራንስፖርትና የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ክላስተር እቅድ አፈጻጸም ቀርቧል።

የህብረተሰቡን ተሳትፎ ያሳደጉ የጽዳት ስራዎች ሞዴል የጽዳት ተቋማትን መፍጠርን ጨምሮ በአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ በሲቪል ምዝገባ፣ እንዲሁም የማታንቀላፋ ከተማ በመፍጠር ሂደት በመብራት አገልግሎት የተከናወኑ ስራዎች አበረታችና የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው መሆኑን ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታትም የጥናትና ምርምር ስራዎች፣ ከተማ አቀፍ ቅንጂት፣ የአመራርና ባለሙያ አቅም ግንባታ፣ የህግና አሰራር ማዕቀፎች ዝርጋታ እንዲሁም የክትትልና ምዘና ስርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ በዘርፉ ሰፊ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዘርፉ በተመዘገቡ ለውጦች ሳይኩራሩ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የበለጠ መትጋትና አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለዚህም አበክረው እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያም አዲስ ሚዲያን ኔትዎርክን ጨምሮ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተጠሪ ሴክተሮች፣ እንዲሁም ለትራንስፖርት እና ማዘጋጃቤታዊ ክላስተር አባል ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

ታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review