የባሕር ዳር ከተማ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የልማት ምሳሌ የምትሆን ከተማ ነች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናልን በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ፣ ባሕር ዳርን የልማት፣ የብልጽግና እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሰፊ ስራዎች ታሪካዊ መሰረታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ባሕር ዳር በታሪክም ሆነ በስነ-ምህዳር ጸጋዎቿ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የልማትና የለውጥ ምሳሌ መሆን የምትችል ከተማ መሆኗን አንስተዋል።

ከተማዋ ከክፍለ ዘመን በፊት ጀምሮ ከማዕከላዊ ሀገር እና ከሸዋ ወደ ሰሜን አካባቢዎች የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከላዊ ድልድይ ሆና ማገልገሏን አስታውሰዋል።

ለዚህም ማሳያ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በጊዮርጊስ ግቢ ማረፊያ ህንፃ የተገነባውና ጎርጎራን ከማዕከላዊ ሀገር ጋር በማገናኘት የንግድ ዝውውር ሲያካሂድ የቆየው ታሪካዊ ቦታ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት በቂ እንክብካቤ ሳይደረግለት የቆየው ይህ አቅም፣ አሁን ላይ ታሪክን መለስ ብሎ በመቃኘት መልካም ጅምሮች እየተከናወኑበት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቱሪዝም ልማት ረገድ በጎርጎራ እና በባሕር ዳር መካከል ያሉትን አካባቢዎችና ደሴቶች ማስተሳሰር የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ከቱሪዝም በተጨማሪ ባሕር ዳር በኢንዱስትሪ መስክ ትልቅ አቅም ያላት ከተማ መሆኗን በማስታወስ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባቱን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋን ይበልጥ ውብ ፣ ሰዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ምቹ እና የሀብት እንቅስቃሴ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችል ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review