AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የህዝብን እና የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ የቡድን ስልጣንን እና ልዩ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ውድቀት ነው።
በአሁኑ ወቅት ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን እያንጸባረቀ ያለው አቋም እና የሚከተለው አካሄድ የዚሁ አውዳሚ መንገድ ግልጽ ማሳያ ሆኗል።
ቡድኑ ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ፍላጎትና አላማን በመንደፍ እኩይ ድርጊቱን ለማስፈጸም ከማንኛውም የሀገር ጠላት ጋር ለመሰለፍ ወደኋላ አለማለቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ቡድኑ ባለፉት አሥርት ዓመታት ያካበተውን ያልተገደበ ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነት በማጣቱ፣ በህዝብ ፍላጎትና በህጋዊ መንገድ ወደ ስልጣን ከመምጣት ይልቅ በትርምስ፣ በጭካኔ እና በኃይል ስልጣን ለመያዝ እየሰራ ነው።
የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች አብሮነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር ከመስራት ይልቅ የብሔር ጥልንና የጥቃት ስሜትን በመዝራት ህዝቦችን እርስ በእርስ ማጋጨት የፖለቲካ ቁማሩ ዋነኛ መሳሪያው አድርጎታል።
ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን የኢኮኖሚ እድገት፣ የልማት ፕሮጀክቶችን እና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማደናቀፍ የታቀደ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ አሻጥር ማካሄድ ሌላው አላማው ነው።
ሕገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የያዘውን አውዳሚ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል።
በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ማደግ እና የነጻነት አቋም የማይፈልጉ፣ ታሪካዊ የሀገር ጠላቶችን ፍላጎት በማስፈጸም የነሱ ተላላኪ በመሆን በማገልገል ላይም ነው።
በሀገር ውስጥ ሰላም እና ህግ ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ፣ ከማንኛውም ጽንፈኛ፣ ሽብርተኛ እና ህገ-ወጥ ቡድን ጋር የጥፋት ጥምረት በመፍጠር ሀገርን የመበተን ሴራ ይሸርባል።
በዲጂታል ሚዲያ እና በውጭ ሀገራት በሚገኙ አክቲቪስቶች አማካኝነት የሀሰት ዜናዎችን እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በመምራት ህዝብን ለማደናገር ይሰራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ወቅት፣ ህወሃት ያቀደው የጥፋት ጥረት በሕዝብና በሠራዊቱ የተቀናጀ መስዋዕትነት የሚመከት መሆኑን በመግለጽ የቡድኑ አውዳሚ ዓላማ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንጂ ለመገንባት እንዳልሆነና ኢትዮጵያ ግን ይህንን ፈተና አልፋ ሉአላዊነቷን አክብራ እንደምትወጣ አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።
የህወሃት ቡድን እያከናወነ ያለው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የመላ ኢትዮጵያውያንን ሰላም፣ ልማት እና አብሮነት የሚጎዳ ነው።
ይህንን የጥፋት አጀንዳ በመገንዘብ፣ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መላው የሀገር ወዳድ ህዝብ በተገቢው ንቃት እና አንድነት ሊቆም ይገባል።
በታምራት ቢሻው