AMN- ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ፤ ሌብነትና ህገ-ወጥ አሰራርን በመከላከል ረገድ መንግስት በሙስና እና ብልሹ አሰራር ላይ የጀመረውን የማያዳግም ርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል።
በመደመር እሳቤ የተቋም ግንባታ እና የሪፎርም ስራዎች በመሰራታቸው አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቀደም ሲል እንዳስታወቀው፤ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በአስተዳደር አካላት እና በልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች ውስጥ የተፈጸሙ ዋና ዋና የሙስና እና አሻጥር ወንጀሎችን ለማረም በተወሰዱት የተጠናከሩ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትን እና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የተሰራውን ስራ በተመለከተ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡
ከንቲባዋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለመታገል በያዘው ቁርጠኛ አቋም በ5 ሺህ 857 አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ተገልጋዮች ላይ ህጋዊ ርምጃ ወስዷል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ 79 ከፍተኛ አመራሮች ፣ 213 የመካከለኛ አመራሮች ፣ 5 ሺህ 430 ባለሙያዎች እና 135 ተገልጋዮች እንደ ጥፋታቸው ክብደት ከማስጠንቀቂያ እስከ ስንብት እና በህግ ተጠያቂ እስከማድረግ የሚደርሱ ርምጃዎች ተወስዶባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ የንግድ ድርጅቶችን ህጋዊነት ከማረጋገጥ እንጻር ሰፊ የክትትል ስራ አከናውኗል።
በዚህም በ231 ሺህ 828 የንግድ ድርጅቶች ላይ የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በተገኙ 24 ሺህ 568 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእርምት ርምጃ መወሰዱ ታውቋል፡፡
ከተወሰደው የእርምት ርምጃ ጎን ለጎን 20 ሺህ 617 የሚሆኑ ነጋዴዎች ስህተታቸውን አርመው ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ አበረታች ስራ መሰራቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
መንግስት ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ከምንጩ በማድረቅ፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ እና የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት በማስፈን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ስለሆነም በዚህ ሂደት የህዝብን ሀብት የሚያባክኑ እና ዜጎችን ለእንግልት የሚዳርጉ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል።
በትዝታ መንግስቱ