አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

AMN – ሰኔ 22/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ እና የኢንዱስትሪ ፓርኩ የኢንቨስትመንት፣ ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲ ፈርመዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ፓርኩ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግና ከስራ እድል ፈጠራ ረገድ ያለዉ ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ‹‹በኢትዮጵያ የተመረተ›› የሚል መጠሪያ በመስጠት የሚያመርቷቸዉ የተለያዩ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና በገበያ ላይ ያላቸው ተቀባይነት ከፍ እንዲል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ፓርኩ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ የኢንቨስትመንት፣ ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲ በበኩላቸዉ በገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻችውን መላክ መጀመራቸዉን ጠቁመዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን የምርት ጥራት እና ተወዳዳሪነት ለዓለም አቀፉ ገበያ ለማስተዋወቅና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማሳየት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በትብብር ለመስራት መወሰኑንም አቶ ዘመን አብራርተዋል፡፡

ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ93 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እና ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡

በካሳሁን አንዱዓለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review