AMN – ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም

በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች አንዱ የሆነው 24 ስፖርት ሜዳ በቅርቡ ከተደረገለት የማሻሻያ ግንባታ በኋላ ለአካባቢው ታዳጊዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በፊት በፊት ሜዳው በክረምት ወራት ጭቃ እየሆነና ውሃ እየተኛበት ለመጫወት ቀርቶ ለመራመድ እንኳን የማያመች፣ በበጋ ወቅት ደግሞ አቧራማ ስለሚሆን ለስልጠናና ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደነበር ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ያስታውሳሉ።
ቀደም ሲል የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስታወሰው ታዳጊ ሙሳብ

ሰይፉ ድሮ ሲጫወቱ በበጋ አፈሩ አቧራ እየፈጠረ ፣ በክረምት ዝናብ ሲዘንብ ጭቃ ይሆን እንደነበረ በማስታወስ ፣ አሁን ግን አርቲፊሻል ስለሆነ ሜዳው ይመቻል ሲል ገልጿል፡፡
የ24 ስፖርት ሜዳ አሁን ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ሜዳው በዘመናዊ የሰው ሰራሽ ሳር ተሸፍኖ፣ በጥሩ ሁኔታ ታጥሮና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ምቹ ሆኖ በመሰራቱ ለአካባቢው ታዳጊዎችና ወጣቶች ደስታን ፈጥሯል።

አሰልጣኝ ወልደአማኑኤል ጸጋዬ ፣ አዲሱ አርቲፊሻል ሜዳ ታዳጊዎች ኳስን በጥሩ ሁኔታ እንዲቆጣጠሩ፣ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና ሙሉ አቅማቸውን እንዲያወጡ ከመርዳቱም በላይ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን በሙሉ እምነት ወደ እግር ኳስ ስልጠና እንዲልኩ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።
ሌላኛው ታዳጊ ተጫዋች ዱሬሳ ነጋሽ የዚህ ሜዳ መሰራት የ

ራሳችንን ችሎታ እንድናወጣ አድርጎናል ይላል።
የ24 ስፖርት ሜዳ እንደዚህ ምቹ ተደርጎ ባይሰራ ኖሩ ለሱስም ተጋላጭ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ነው የገለጸው፡፡
የሜዳው አለመመቸት በልምምዳቸው ላይ ጫና ያሳድር እንደነበር የጠቀሰው ታዳጊ ነቢል ጥላሁን አሁን ግን የሜዳው መገንባት የእግር ኳስ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ እንዳገዛቸው ገልጿል።
በሜዳው ልምምዳቸውን የሚያደርጉ ታዳጊዎችም ትልቅ ህልማቸውን ሰንቀው እየሰሩ ይገኛሉ። የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሆነው ሀገራቸውን ለመወከልም እየታተሩ ይገኛሉ።
የቦሌ 24 ስፖርት ሜዳ አርቲፊሻል ሳር መልበሱ የታዳጊዎችን የእግር ኳስ ክህሎት ለማዳበር እና ከአልባሌና ከሱስ እንዲቆጠቡ አስችሏል፡፡ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፈራትም ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
በታደሰ ሽፈራው