በከተማችን በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዮብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዮብ ፍሳሽ የሚያጣራ የኮዬ ፍሳሽ ዘመናዊ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን አስመርቀን አገልግሎት አስጀምረናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዮብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዮብ ፍሳሽ የሚያጣራ የኮዬ ፍሳሽ ዘመናዊ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን አስመርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በቱሉ ጉዶ፣ ለገዳዲ ክፍል 2፣ በረከት የጋራ መኖሪያ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳና ሌሎችም በርካታ ጉድጓዶችን አልምተን በከተማችን ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው 525 ሺህ ሜትር ኪዩብ በቀን የማምረት አቅም ዛሬ ላይ 910 ሺህ ሜትር ኪዩብ አድርሰናል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ለረጅም ዘመን በከተማችን የሚገኙ ወንዞች በፍሳሽም፤ በደረቅ ቆሻሻም ሲበከሉ ቆይተዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ ይህን ችግር ለመፍታት የፍሳሽ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና የማጣራት አቅምን ለማሳደግ ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ በሰጠነው ከፍተኛ ትኩረት በ2009 ዓ .ም በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ የነበረው ፍሳሽ የማጣራት አቅማችን የዛሬውን ጨምሮ ከ253 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ማሳደግ ችለናል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የነዋሪዎቻችንን ጤናና ንጽህና የሚጠብቁ፣ የወንዞቻችንን ብክለት የሚቀንሱ፣ የአካባቢ ጥበቃችንን የሚያጠናክሩ ናቸውም ብለዋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ውብ፣ ጽዱ፣ ጤናማ፣ አረንጓዴ፣ ዘመናዊና ለትውልድ የምትመች ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ግብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት።

ይህን ታላቅ ፕሮጀክት እውን ላደረጋችሁ፤ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የብድር አገልግሎት እየሰጠን ያለውን የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የውሃው መገኛ አካባቢዎችን በትብብር እንድናለማ ላገዘን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ ከሁሉ በላይ ዘላቂ ኑሯቸውን ሲመሩበት የነበረውን መሬት ለዚህ ታላቅ ልማት የለቀቁ አርሶ አደሮች እና ለፕሮጀክቱ ስኬት ሌት ተቀን ያለእረፍት የተጉ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አመራሮች እና ባለሙያዎችን በራሴና በከተማ አስተዳደራችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review