AMN- ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም

አርሷደሮቹ የአካባቢን አንጻራዊ የልማት ጉልበት መለየት እና ወደ አትራፊ እና ዘላቂ የግብርና ጎዳና መሸጋገር ይገባል የሚለውን ሃገራዊ መርህ እና ስምሪት ተግብረው አሳይተዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ ከዚህ ቀደም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምርቃት ላይ ባስተላለፉት ታሪካዊ መልዕክት “ሐይቅ የታሪክ ብቻ ሳይሆን የፍራፍሬ ልማት፣ የተትረፈረፈ ምርት፣ የውበትና የጥጋብ ሥፍራ መሆን አለባት” ብለው ነበር ብለዋል።

ዛሬ የርሳቸው ቃል ፍሬ አፍርቶ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ተሁለደሬ ወረዳ የጎበያ ቀበሌ በአትክልት እና ፍራፍሬ ክላስተር ተሸፍኗል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ የልማት ትጋት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ሉዓላዊነት ተደማሪ ጥሪት እና ወረት ነው በማለትም ነው ያከሉት።
መንግሥት ለዚህ ልማት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለም አፈር፣ ንጹሕ ውኃና ሥራ ወዳድ ሕዝብ ባለበት ምድር፣ በተቀናጀ ዐቅም ተግተን ከሠራን ብልጽግና ሕይወት፣ ድህነት ታሪክ ይሆናል ብለዋል።