የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ

AMN- ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ፤ 2018 ዓ.ም ስኬታማ ሥራዎች የተሰሩበት፣ ተቋማዊ መሠረት የተጣለበት እና አሰራሮች የተሻሻሉበት ዓመት ነበር ብለዋል።

በዚህም በሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ የግዢ ንብረት ሎጀስቲክስ አስተዳደር ምክር ቤቱ ስኬት ያስመዘገበባቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ያለፈው ዓመት ሥራዎች እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸው የ5 ዓመት ስትራቴጂክ የሥራ አመራር አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ ያገኛቸውን ስኬቶች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ ይጠበቃል።

በጉባዔው ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፤ ጥሪ የተደረገላቸው ታላላቅ ዓሊሞችና ኡስታዞች እንዲሁም የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተገኝተዋል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review