AMN- መስከረም 2/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ የቆየ ጥልቅ ወዳጅነት፣ ትብብር እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፡፡
ይህ የዘመናት ግንኙነት እና በሕዝቦች መካከል ያለው ጠንካራ ወዳጅነት በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ መጥቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ የሚባለውን ዲፕሎማሲ የጀመሩት በ1948 ዓ.ም ሲሆን ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ሀገራት በኒው ዴልሂ ኤምባሲዋን የከፈተች የመጀመሪያዋ ሀገር በመሆን ታሪካዊ አሻራ አኑራለች። ይህ ግንኙነት በ1952 ዓ.ም በአምባሳደር ደረጃ ከፍ ብሎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
በኢኮኖሚው መስክ የሁለቱ ሀገራት ትብብር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ሕንድ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ቀዳሚ ምንጭ ሀገር ሆናለች፡፡
ሕንድ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፎች የሚደረጉ ማሻሻያዎችን በመደገፍ ዘላቂ ወዳጅነቷንም አጠናክራለች፡፡
በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘላቂ ልማት ጉዳዮች ላይ የጋራ ትብብራቸውን ይበልጥ አሳድገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ “ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሕንድ ኒው ዴልሂ ገብተዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይታቸውም የመከላከያ ትብብርን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ የማዕድን ልማት እና ወደ ኮፕ 32 (COP 32) በሚደረገው ጉዞ ላይ ሀገራቱ ያላቸውን አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት መክረዋል፡፡
ውይይታቸውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ኢትዮጵያና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር፣ የዘመናት የባህል ግንኙነት እና በሕዝቦቻችን መካከል ጠንካራ ወዳጅነት አለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ደማቅ አቀባበል ያደረጉት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ሕንድ የረጅም ጊዜ ወዳጅነታቸውን ወደ አዲስ የትብብር ዘርፎች እያሸጋገሩ መሆናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
ሕንድ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ጥያቄዋን በጠንካራ ሁኔታ ከደገፉ አባል ሀገራት አንዷ ስትሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥም ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሻሻል የጎላ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በታኅሳስ 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ታሪካዊ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ምዕራፍ ያሸጋገረ ነበር፡፡
በትዝታ መንግስቱ