አዲስ አበባ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የታቀዱ ግቦች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት እውን ይሆናሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የጤና አገልግሎቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳደግ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የተያዙት ግቦች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚረጋገጡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ 5 ዓመታት ዕቅድ እና የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ውይይት ማጠቃለያ ላይ የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል።

በከተማዋ የመንግሥትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና መስጠት የሚችሉበትን አቅም መገንባት ዋናው ግብ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር ሳይሄዱ በሀገራቸው ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል እውን የሚያደርግ እንደሆነ አስረድተዋል።

መንግሥት ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት አርአያ ሆኖ እያሳየ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች ከዚህ ቀደም በምሥራቅ አፍሪካ በኬንያ ብቻ ይገኝ የነበረውን የፔት ስካን ቴክኖሎጂ በላፍቶ ሆስፒታል እንዲገባ መደረጉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ይህን የመንግሥት ሥራን ተከትሎም በቅርቡ የግል ህክምና ተቋምም መሳሪያውን ማስገባቱን አብራርተዋል።

የመንግሥት አቅጣጫና ቁርጠኝነት የተፈለገውን ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጠቆሙት።

ከንቲባዋ የጤና ቱሪዝም መዳረሻነት ለእኛ ነዋሪዎች፣ ለአጠቃላይ ለኢትዮጵያውያን፣ ቀጥሎ ደግሞ ሌሎች እዚህ ከተማ ላይ የሚኖሩ የውጪ ዜጎች እና ለሥራም፣ ለኮንፈረንስም የሚመጡ የከተማችን እንግዶች የሚተማመኑበት፣ ለህክምናም የሚመጣበት ከተማ ማድረግ እስከ አምስት አመት ድረስ ሙሉ ለሙሉ የምናረጋግጠው ስራ ነው ብለዋል፡፡

ለስኬቱም አቅጣጫዎችን በትክክል ለይቶ ቅድሚያ በመስጠት፣ በቁርጠኝነት በማቀድ እና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በታደሰ ሽፈራው

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review