AMN- ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም

ለመጪው አዲስ ዓመት የሚከናወኑ የቁም እንስሳት እርዶችን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችል አጠቃላይ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ። ተቋሙ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሚሽነር አህመድ መሀመድ፤ በአዲሱ ዓመት በዓል ከ4 ሺህ 500 በላይ የቁም እንስሳትን እርድ ለማከናወን ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል ከ3 ሺህ በላይ በሬዎች እና ከ1 ሺህ 500 በላይ በግና ፍየሎች እርድ እንደሚከናወን ታቅዷል።

በአገልግሎቱ መሰረትም ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ በግና ፍየልን በ300 ብር፣ እንዲሁም በሬዎችን ደግሞ በ2ሺ 100 ብር የቄራ የእርድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ተጠቁሟል።
ሕብረተሰቡ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ጤናማነታቸውና ጥራታቸው የተጠበቁ ሥጋዎችን በንጽህና እንዲያገኝ ወደ ቄራዎች ድርጅት መምጣት እንደሚገባው ጥሪ ቀርቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶ/ር ፀጋ ለማ በበኩላቸው፤ ማህበረሰቡ ከልኳንዳ ሥጋ ሲገዛ በቄራ መታረዱን መጠየቅና ማረጋገጥ እንደሚገባው አሳስበዋል።
እንዲሁም በቅርጫ ወቅት የሚታረዱ የቁም እንስሳትን ጤንነት በቦታው በመገኘት ለመመርመር ተንቀሳቃሽ ቄራዎችን በቀጣይ ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ መኖሩን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ማህበር ለአዲስ ዓመት በዓል ወደ ከተማዋ የሚገቡ የቁም እንስሳት በቂ መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ሕገ-ወጥ እርዶችንና ጤናማ ያልሆኑ አሰራሮችን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
በወንድምአገኝ አበበ