የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባዛር ተከፈተ

You are currently viewing የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባዛር ተከፈተ

AMN – ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም

በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የተዘጋጀው የዘመን መለወጫ በዓል ባዛር በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ደበላ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተከፈተ።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ፀጋዬ፣ የከተማ አስተዳደሩ በዋጋ ንረት ቅነሳ እና በንግድ ሥርዓቱ ፍትሃዊነት ዙሪያ ተጨባጭ ውጤቶች ያስመዘገቡ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው፣ በዓሉን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ ምርት በሚያከማቹና በሚደብቁ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።

አያይዘውም በባዛሮቹ ላይ በቂ ምርት መቅረቡን ጠቅሰው፣ የከተማው ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ባዛሮች በመገኘት እንዲገበያዩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቢሮው የሚያዘጋጃቸው ወቅታዊ የበዓል ባዛሮች በበዓላት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት በመከላከል ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል።

እነዚህ የንግድ ትርኢቶች እና ባዛሮች ከዛሬ ነሐሴ 28 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሕብረተሰቡ ክፍት ሆነው አገልግሎት እንደሚሰጡ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review