AMN – ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ከልማት ጋር በማቀናጀት በተሰራው ስራ የአዲስ አበባ ወንዞች ተፈጥሯዊ ውበታቸውንና ንፅህናቸውን በመላበስ የከተማዋን ስነ-ምህዳር እየጠበቁ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ አረንጓዴ እና በንፁህ ወንዞች የታደለች ከተማ እንደነበረች ቢነገርላትም ከለውጡ በፊት የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 2 ነጥብ 8 በመቶ በማሽቆልቆል ከፍተኛ የስነ-ምህዳር አደጋ ተጋርጦባት ነበር፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ከወንዝ ዳርቻ ልማቶች ጋር በማቀናጀት በተሰሩ ስራዎች የአዲስ አበባ ወንዞች ተፈጥሯዊ ውበታቸውንና ንፅህናቸውን ዳግም በመላበስ የነዋሪዎችን ጤና እና የከተማዋን ስነ-ምህዳር እየጠበቁ ይገኛል፡፡
የለውጡ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ እና የተቀናጀ የልማት ፖሊሲ ከወንዝ ዳርቻዎች ልማት ጋር ተዳምሮ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 24 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡
የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደርን ከመሰብሰብና ከመጣል ባህላዊ ልማድ በማውጣት ወደ መልሶ መጠቀም በመሸጋገሩ የከተማዋ ወንዞች ከብክለት ድነው ንፁህና ማራኪ የህዝብ መዝናኛ መሆን ችለዋል፡፡

ይህም የስነ-ምህዳር፣ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ስኬት አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ውበትና ንፅህና እንድትላበስ በማድረግ ከአፍሪካ 10 ጽዱ ከተሞች አንዷ ለመሆን እንድትበቃ ትልቁን ድርሻ አበርክቷል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ይህን የወንዞች እና የስነ-ምህዳር መነቃቃት ለማምጣት በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በተለይም ቆሻሻን ወደ ሀብት የመቀየር ስራ ተጠቃሽ ነው፡፡
በመዲናዋ ባለፉት አምስት አመታት ከ5 ሚሊየን ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብ የከተማዋን ገፅታ መቀየር የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 484 ሺህ 632 ቶን የሚሆነው ቆሻሻ ወደ ኡደት ገብቶ ለንፁህ ኢነርጂ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች መልሶ ጥቅም ላይ መዋል መቻሉን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በትዝታ መንግስቱ