AMN መስከረም 26/2019

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባቸውን ያካሄዱ ሲሆን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተዉ ንግግር አድርገዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የሚያከናዉኗቸዉ ተግባራት እና የሚደነግጓቸዉ ህጎች በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ የሥልጣን ፍኖት በህዝብ ይሁንታና ቅቡልነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የተጣለባቸዉ ህዝባዊና ሃገራዊ ሃላፊነት በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመረጣችሁ ህዝብ ከአመኔታ ጋር ታላቅ አደራን የሰጣችሁ በመሆኑ ይህንን ሃላፊነት በታላቅ አስተዋይነት፤ ጥበብ ፤ ብልሃትና ታታሪነት እንደምትወጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያምናል ነዉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸዉ፡፡
የምክር ቤቱ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ይህንን አደራ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ጭምር ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የምክር ቤቱ አባላት ለተፈጻሚነቱ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ቀዳሚ ትኩረት መልካም አስተዳደርን የሚያዘምን ፤ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ እና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ መሆን ይገባዋል ነዉ ያሉት፡፡
ምክር ቤቱ የኑሮ ዉድነትን የሚገራ ፤ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ይበልጥ የሚያስፋፋ፤ የመሰረተ ልማት አዉታሮችን በስፋት የሚዘረጋ እና የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያጸና ሊሆን እንደሚገባዉም ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ