የመስቀል ደመራ በዓል ድባብ ማድመቂያዎች

You are currently viewing የመስቀል ደመራ በዓል ድባብ ማድመቂያዎች

AMN – መስከረም 16/2019

የክረምቱ ጭጋግ ተገፎ መስከረም ሲጠባ ምድር በቢጫ አደይ አበባ ስታጌጥ፣ የአሪቲና የቄጠማ ውብ መዓዛ አየሩን ሲቆጣጠሩት፤ ኢትዮጵያውያን ታላቁን የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እያከበሩ ይገኛሉ።

ጋራውና ሸንተረሩ በቢጫ አደይ አበባ ፈክቶ የሰላም፣ የፍቅር እና የዘመን መለወጫ ማብሰሪያ ሆኖ ይቀርባል። በገጠርም ሆነ በከተማ መንገዶች ዳር የሚታየው ይህ ተፈጥሯዊ ውበት የሕዝቡን መንፈስ በማደስ አዲስ ተስፋ እንዲላበስ ያደርጋል።

በቤቶች ውስጥ ቄጠማና አሪቲ ተዘጐዝጉዞ፣ የዕጽዋቱ መዓዛ የቤተሰቡን ትስስር አጠናክሮ የሞቀ የበዓል ድባብን ይፈጥራል። በዩኔስኮ (UNESCO) የዓለም የማይዳሰስ የባህል ሀብትነት የተመዘገበው ይህ በዓል፤ የኢትዮጵያውያን ሰብአዊነትና የአብሮነት መገለጫ ነው።

ፀሐይ ስትጠልቅ ሕፃናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ችቦዎችን አብርተው ወደ አደባባይ በመውጣት በሚያሰሙት የደስታ ድምፅና እልልታ አየሩን በድምቀት ይሞሉታል። የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የሕዝብን ማንነት፣ ባህል፣ ተፈጥሯዊ ትስስር እና ማኅበራዊ እሴቶች ተደምረው ኢትዮጵያን በልዩ ውበት ያስጌጧታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review