AMN መስከረም 20 / 2019
በህንድ መከላከያ ሚኒስቴር ስቴት ሚኒስትር እና ጆይንት ሴክሬተሪ ሚስተር ሳንጃይ ኩማር የተመራው ልዑክ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚን የመማር ማሥተማር ሂደት ጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ጌታቸው ሀብታሙ በጉብኝቱ ወቅት ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት እና ትብብር ያላት ሃገር መሆኗን ገልፀው በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ወታደራዊ አካዳሚው ሲመሰረት ህንድ በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን አውስተዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካደሚ ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ወታደራዊ አካዳሚ በመጎብኝታቸው ደስተኛ መሆናቸው ገልጸዋል።
ከጎብኝዎች መካከል በኢትዮጰያ የህንድ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዲየር ጄነራል ሰሚር ማድህግል፣ የህንድ ዓለም አቀፍ ትብብር ቡድን ዳይሬክተር ኩውሽርሌንድ ፐርት እና አሽሽ ሻርማ ይገኙበታል።
በልዑካን በድኑ እና በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ መካከል የስጦታ ልውውጥ ማድረጉን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመላክታል፡፡