AMN – ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም
በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የነበረው 12ኛው ዓለም አቀፍ የጣና ፎረም በስኬት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባወጣው መግለጫ፣ መርሐ ግብሩ በስኬት ተጠናቆ እንግዶች ወደ መጡበት እስኪመለሱ የተቀናጀ የፀጥታ ማስከበር ሥራ መከናወኑን ገልጿል ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የጥበቃ፣ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር እና የቅድመ-ወንጀል መከላከል ሥራዎችን በትኩረት ሲያከናውን ቆይቷል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም የደህንነት ተቋማት ሌት ከቀን የላቀ ሙያዊ ምግባር በማሳየት ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና ላሳዩት የላቀ የሕዝብ ወገንተኝነት ዋና ጠቅላይ መምሪያው ምስጋና አቅርቧል።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች ለአካባቢያቸው ሰላምና ደህንነት ቁርጠኛ በመሆን፣ የጸጥታ ኃይሉ የሚሰጣቸውን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ በመተግበርና ለእንግዶቹ ተገቢውን አክብሮት በማሳየት ላደረጉት ከፍተኛ ትብብርም መምሪያው ምስጋና አቅርቧል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሁንም በክልሉ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የጀመረውን የተቀናጀ የህግ ማስከበርና የህዝብ ደህንነት የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።